የአባወራ (patriarchal) ስርዓት ሽፋን ሲጋለጥ
የኃይል ፣ የስልጣን ፣ የቋንቋ ላይ ተፅዕኖዉ እና በኢትዮጵያ የፆታ ነፃነት ትግልን ስንቃኝ
የአባወራ/አባታዊ መዋቅራዊ ስርዓት ስንል ምን ማለታችን ነው
“The demand of recognition when denied, become a demand of power” Francis Fukuyama
ሰው በተፈጥሮው መታየት እውቅናን ማግኘት ይፈልጋል ይህ ደግሞ ክፍ ነገር አይደለም ችግሩ አንዱ አካል ሌላውን ረግጦ እና የሌላው የሉዓላዊነት እውቅና ነስቶ ራሱን የበላይ ሲያደርግ ነው የአባወራ መዋቅራዊ ስርዓት ይህ ነው፡፡ ወንድነትን ስፍራ መስጠቱ አይደለም ችግሩ ነገር ግን ሴትነትን መርገጡ እና ይሁን ብሎ ካሰመረው ልክነት ውጪ ያሉ ሌሎች ማነንቶችን እውቅና መንሳቱ እና ማፈን መጨቆኑ ነው፡፡
በዚህ ፅሁፍ አባታዊ ስርዓት የሚለውን በብዛት ያልተጠቀምኩት አባትነት ስለ ገዢነት ስላልሆነ ነው ፡፡ የአባወራ ስርዓታዊ መዋቅር ስላ አካላዊ ጾት ወንድነት ብቻ አይደለም ስለ ማህበረሰባዊ፤ ባህላዊ፤ ሀይማኖታዊ ስፍረዎችን ሁሉ ጥሶ የራሱን የወንድን የበላይነት የሚያገዝፍ ስርዓት ስለሆነ ነው፡፤ ከዚህ ቀደም ስል ውስጣዊ አፈና/ጭቆና በተመለከትን ጊዜ ምን ያህል እነዚህ መዋቅራዊ ስርዓቶች ሰዎችን እንደሚያፍኑ እና እንደሚጨቁኑ ተመልክተናል ይህ የጭቆና ስልት የሚቀዳው ደግሞ ከ አባወራ መዋቅራዊ አስተሳስብ ነው፡፡ አንድ ነገር ለማፍን የምናፍንበት ስርዓት ያስፍልጋል ይህ አፋኝ ስርጫት አባወራ ስርዓት ነው፡፡
ነገር ግን ምን ማለታችን ነው የአባወራ ስርዓት ስንል በአጭሩ ወንድን የማህብረሰቡ፣ የተፈጥሮ፣ የስኬት፣ የውሳኔ፣ የአመራር ነገሮች ሁሉ ቁንጮ አድርጎ የሚያስቀምጥ አስተሳሰባዊ ምልከታ ሲሆን ሴቶችን ለወንድ ተገዢ እና የበታች እንደሆነች አድርጎ የሚስል መድሎ እና ውሸት ላይ የተመሰረተ ስርዓት ነው ከሴቶችም አልፎ ትልልቅ ወንዶች በታዳጊ ወንዶች ላይ ስልጣን የሚጭን ፣ በስልጣን ተዋረድ የተገነባ፣ ከፍፍልን የሚያራምድ፣ የኃይል ተዋረድ ላይ የቆመ አስተሳሰባዊ አገዛዝ ነው።
ይህ አስተሳሰብ ሴቶች ደካማ ናቸው፣ ሊታመኑ የማይችሉ ናቸው፣ የውድቀታችን ምክንያት ናቸው፣ ስሜታዊ ስለሆኑ መምራት ሳይሆን መመራት ያለባቸው ናቸው የሚል አስተሳብ በባህል ውስጥ፣ በሀይማኖት ፣ እንዲሁም በማህበረሰቡ መዋቅር ፣ውስጥ አስርፆ ያስገባ ነው፡፤ ስርዓት ወይ መዋቅር ወይም አስተሳሰብ ብንለው የሶስቱንም አይነት ይዘት ያለው ስለሆነ ነው፡፡
አባወራ መዋቅር መፈጠር ምክንያቶች
ችግሩ ከዘመን ጅማሬ የነበረ የተፈጥሮ ቀመር እንደሆነ ተደርጎ እስኪታሰብ ድረስ የተገነባ ማህበረሰባዊ መዋቅር ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ ፈጣሪ እንደ ማስረጃ እየቀረበ ወንድን እንዲገዛ ሴት እንድትገዛለት ነው የተፈጠርነው የሚል እድምታ የሚያሰራጭ ነው (ሀይማኖታዊ ቀነኖናዎች አስተምህሮቶች አብዛኛው ከአውዱ ተፋተው አባወራ ስርዓት እንዲደግፉ ተደርገው የተሰራጩ እንደሆኑ የአደበባይ ሚስጥር ነው)
የሆነው ሆኖ የአባወራ አስተሳሰባዊ መዋቅር እንዴት እና በዚ ዘመን ጀመረ ብለን የምንናገረው አይደለም ነገር ግን ከከተሞች መመስረት ጋር እንደጀመር የስነ-ሰብዕ እና የማህበራዊ ሳይንስ አጥኚዎች ይናገራሉ፡፡ የመጀምሪያዋ ከተማ ስልጣኔ ምትባለው ሜሴፖታሚያ (የአሁኑ ኢራቅ ፣ ቱርክ፣ ሲሪያ / 5000 ዓ.ዓ ገደማ) ለነበረው የስልጣኔ መሳካት ሁሉም የተሰመረ ስፍራ እና ማህበረሰባዊ ሚና እንዲኖረው ግድ ነበር፡፤ በዚህም ወንዶች ሀገሩን መጠበቅ፣ መዋጋት፣ ወይም መገንባ ሊሆን ይችላል እዛ ላይ ሚናቸው ጎልቶ ሲወጣ( አካላዊ ጥንካሬ ለዚ ምክንያት ሆኖ መጠቀስ ይችላል) ሴቶች የህዝብ ቁጥርን መጨመር ግዴታ ስለነበር ዘር መተካቱ እና የቤት ነገሮች ላይ ትኩረታቸው እንዲገደብ ተደረገ ፡፡
ከስልጣኔ እና ክግብርና ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ይህ ስርዓት ሴቶች የነበራቸውን ነፃነት በመሻር መሰረቱን ጣለ ይህ ደግሞ ወንዶች ያፈሩት የነበረውን ንብረት ቀጥታ ለልጆቻቸው እንዲያወርሱ በሚያስችል መንገድ መዋቅር መፈጠር ነበረበት በዚ ዘመን ልጆች በእናታቸው ዘር ግንድ ከመጠራት ይልቅ የአባታቸውን ስም እና ዘር ሀረግ መከትል እንደጀመሩ እንደ ጌርዳ ሊንር እና ፍሬድሪክ ኤንጅል ያሉ ተመራማሪዎች ይመስክራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩ ማህበረሰቦች ልክ እንደ ካታልሆዩክ (አሁናዊ ቱርክ ወደ 9000ዓ/ዓ) ገደማ የነበረ ታላቅ ግዛት የነበረው ማህበረሰባዊ መዋቅር ስለ ፆታ ግድ የማይላቸው እና ሴቶችም ከወንድ እኩል ማህበራዊ ሚና ነበራቸው፣ አመራር ላይ ፣ንግድ ላይ ይሳተፉ የነበሩ፣ ከዛም ባስ ሲል አካላዊ ልዩነታቸውም ይሃን ያህል የሰጠ እንዳልሆን የስነ-ቁፋሮ ተማራማሪዎች ያገኙት መረጃ ያሳያል፡፡ እንደ ጥንታዊ አፍሪካ ማህበረሰቦች ጊኒ፣ የጋና አሳንቴ ማህበረሰብ ፣ የማሶኡ ብሄሮች እንዲሁም በእስያ እና አውሮፓ ከ160 የሚበልጡ ማህበረሰቦች በእናት በኩል ስልጣን ኃይል እና ንብረት ይተላለፍ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የአባወራ መዋቅር በማህበረሰባዊ መዋቅር ውስጥ የሴቶችን ስልጣን እና ቦታ ለመገደብ ክፍተኛ አስተዋፆ አድርጓል ምክንያቱም ሴቶች እንዲወልዱ እና ልጆን እንዲያሳድጉ እና ለባሎቻቸው የሚያስፈልገውን ነገር እንዲያሟሉ ከዛም እየጠለቀ ሲመጣ የአባወራ መዋቅር አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን ማህበረሰባዊ ስርዓት ሲሆን ሴቶች ለወንዶች እንደንብረት መቆጠር እንዲጀምሩ እና ፍፁም ነፃነታቸውን ሴትነታቸውን እና ፆታዊነታቸውን ሳይቀር ወንድ እስኪወስን ሰብዓዊ ክብራቸውን እንዲነጠቁ ምክንያት ሊሆን በቅቷል፡፡
ይህ መዋቅር ለምን እንቃወመዋለን
“A society that fails to recognize the dignity of its entire member or that suppresses their true identities breed resentment and instability. People cannot flourish when they are forced to deny who they are” Francis Fukuyama
አሁን ላይ ምን ችግር አለ ሴቶች ከተጉ የፈለጉትን ነገር ማድረግ ይችላሉ ነጻነቱ አለ ማንም ሴትን ባሪያ ነች ወይ ንብረቴ ናት ብሎ የሚያስብ የለም ሀብት ማፍራ ፣ፖለቲካ ላይ መሳተፍ፣ ብቻ የወደዱትን ማድረግ ይችላሉ ልንል እንችላን በተወሰነ መልኩ እዚህ ነገሮች ተሳክተዋል ምንም እንኳ ደም ተፋሶ የመጣ እንደሆነ ሳንረሳ ማለት ነው፡፡
ይህን ጥያቄ ራሱ ከጠየቅን ችግር አለብን ብዬ አስባለው ምክንያቱም እያወራን ያለነው ስለ ስርዓታዊ መዋቅር ነው የተወሰነ ለውጦች አይተናል ማለት ስርዓቱ ትከክለኛ ነው ማለት አይደለም ወይም በማህበረሰብ ውስጥ የፈጠረው ተፅዕኖ ጠፍተዋል ማለት አይደለም ፡ ቀጥዬ የተወሰኑ ምክንያቶችን ለማንሳት ሞክራለው ይህን ስርዓት እስኪወገድ መቃወም ለምን እንደሚስፈልግ
• የአባወራ ሰርዓት ስለ አባት(ወንድ) ህግ ወይም አመራር ብቻ አይደለም ይልቅ መወቅሩ ስለ ቁጥጥር እና ሰዎችን ግላዊ የመወሰን አቅም የሚነጥቅ እና በእነሱም ላይ ፈላጭ ቆራጭ የመሆን መብትን ለሌሎች ስለሚሰጥ ነው፡ ይህ ለሌሎች የተባለው ሰው ሴት/ወንድ/ድርጅት/መዋቅር/ማህብረሰብ/ሀይማኖት ወይም ምንም ሊሆን ይችላል መሰረቱ ግን ወንድነትን በማግዘፍ ቢሆንም ማለት ነው፡፡
• በ2021 የአለም አቀፍ የሰራተኞች ድርጅት እንደወጣው መረጃ 60-76% የአለም ስራ ሰዓት በሴቶች የሚሸፈን ሲሆን አጠቃላይ ሴቶች ከአለም አቀፍ ገቢ የሚሸፍኑት 10% አይሞላም ይህም አሁንም ምን ያህል የጉልበት ብዝበዛ እንዳለ ነው፡፤ ስራ መስራት መቻል ብቻ ሳይሆን ለሰሩት ስራ ትከክለኛ ደሞዝ መከፈል መቻልም ነው የአባወራ ስርዓት አንድ አይነት ሚና ላይ ለወንድ እና ለሴት የሚያቀርበው ክፍያ የተለያየ ነው ፡፡ ምክንያቱም ወንድ የበለጠ ይገባዋል የሚል አስተሳሰብ ስለተፈጠረ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ይህ ድርጅት ባወጣው ሌላ መረጃ 22 ሚሊዮን ሰዎች ሳይፈልጉ በትዳር ውስጥ ያሉ ሲሆን ከእነዚ መሃል 15ሚሊዮን ገደማ የሚደርሱት ሴቶች እና ታዳጊ ልጃገረዶች ናቸው ፡ ልብ በሉ ወንዶች ላይ የሚደርሰውን ግፍም እያቀለልን አይደለም ይልቅ ምን ያህል ሴቶች የበለጠ በዚህ ጨቋኝ መዋቅራዊ ስርዓት ከወንዶች በላይ ለጉዳት ተጋላጭ እንደሆኑ ነው፡፡ ሌላው መነሳት ያለበት ክፍያ የሌለው ስራዎችን በተመለከተ በወጣው ILO report ሴቶች 76.2% የሚሰሩ ሲሆን ወንዶች የተቀረውን ይይዛሉ ይህ ምን ያህል ሚዛን አለመኖር የሚያሳይ ነው ሲቀጥል ሴቶች በቀን ውስጥ ረዥም ሰዓት ከወንዶች በላይ እንደሚሰሩ(የተከፈለም ያልተከፈለም ስራ ተዳምሮ) መረጃዎቸ ያሳያሉ
• ሌላው ይህ አባወራ አስተሳሰብ የፈጠረው የወንድ የሴት ባህሪ የሚሉ ተፈጠሮ ናቸው ተብለው የሚታመኑ የሰውን እውነተኛ ተፈጥሮ የሚነሱ አስተሳሰቦች ናቸው ፡፡ ሴቶች ትንከባካቢ ተፍጥሮ ነው ያላቸው ስሜታዊ ናቸው በምንልበት ሰዓት ወንዶች ስሜት የሌላቸው እና መንባከብ የማይችሉ እንደሆኑ ይናገራል ይህ ደግሞ ወንዶች በዚ አይነት እምነት በማደግ ስሜታቸውን የሚያፍኑ እና መንባከብ ወንድነታቸው እንደማይፈቅድ በማመን ይኖራሉ፡፡ ይህም ወንድነት እና ሴትነት ምን እንደሆኑ ሰዎች ለራሳቸው ራሳቸውን ከመበየን በመከልከል የተሰመረላቸውን ሚና እና ማንነታዊ ጭምብል እንዲለብሱ ያስገድዳል፡፡ ትርፉ ምንድነው ካልን ራሱን ያልሆነ ሮቦት የሆነ ነህ የተባለውን የሚኖር ደስታ የሌለው ሰው መፍጠር ነው፡፡
• ጨቋኝ አፋኝ የሆን ስርዓት በአንድም በሌላም እፈናው በተቃውሞ መውጣቱ አይቀርም፡፡ ማህበረሰብ ምንድነው ?ከግለሰቦች ካልተገነባ በቀር ሊመሰረት አይችልም የእያንዳንዱን ሰው ግለሰባዊ ማንነት ጨፍልቆ ማህበረሰብ መሆን አይቻልም ፡፡ የአይደንቲቲይ የተሰኘው መዕሐፍ ጸሐፊ ፍራንሲ ሰዎች ሁለት ማንነት አላቸው ይለናል ውስጣዊ እና ውጫዊ አብዛኛው ጊዜ ውስጠዊው ከውጪ ጋር በምን የማይገናኝ ነው ምክንያቱም ውጫዊው የተሰጠን ሚና ነው እንድንሆነው የሚጠበቀው (የሆነ እድሜ ላይ አግቡ እንሚባለው) ይህ ደግሞ የማንነት ጥያቄን ይፈጥራል ሰውን ቀውስ ውሰጥ ሊከት ይችላል ፍራንሲ ብዙ ማህረሰቦች እና መንግስታት ይህን ውስጠዊ ማንነት እውቅና መስጠት ሳይችሉ ሲቅር ጦርነት ሽብር እና አለመግባባቶች እንደሚፈጠሩ ይጠቅስልናል፡፤ ይህ ሁሉ የመጣው ለምንድው ብንል ማህበረሰቡ ተመሰረተበት መዋቅር መልሳችን ይሆናል
• ሌላው የአባወራ መዋቅር ራሱን ለማስቀጠል እና ለማኖር የሚጠቀማቸው እርምጃዎች ናቸው ከእነዛ መሃል ሴክሲዝም፣ ክላሲዝም፣ ሄትሮሴክሲዝም ፣ የሀይማኖተኛ ፅንፈኝነት ናቸው እነዚህ አስተሳሰቦች አባወራ የተመሰረተበትን የወንድን የበላይነት ለማስጠበቅ እጅ እና ጓንት ሆነው የሚስሩ ናቸው፡፡
ቋንቋችን
የአባወራ መዋቅርን ለምን መቃወም አለብን ከሚለው ርዕስ ሳንወጣ ቋንቋችን ምን ያህል አስተሳሰባዊ መድሎ እንዳለው እንድንረዳ ፈልጋው ሰው ራሱን ለመግለፅ እና ለመበየን የሚጠቀምባቸው ቃላት አሉታዊ ከሆኑ ስለራሱ የሚኖረው አመለካከት የተዛባ ይሆናል:: ‹‹ሴታሴት›› የሚለው ቃል ለወንድ በመጠቀም የበታች እንደሆነ ለስደብ በሚጠቀም ማህበረሰብ መሃል እየኖርን መዋቅራዊ ስርዓቱ የፈጥረው ምልከታ መገንዘብ ይቻለናል፡፡ ሴታሴትነት እንደ ደካማነት እና የበታችነት እየታየ ወንድ የሴት በተባሉ በተገደቡ አስተሳሰባዊ ሳጥኖች ውስጥ ያሉ ባህሪያዊ ዝንባሌ ሲያሳይ ሴትነትን እንደ ስድብ መጠቀም የቃላቶቻችን ጥቅም ምን ያህል እንደተበረዙ ያሳያል:: በተቃራው ጠንካራ ፣ጀግና ወይም ደግሞ ብርቱ ነገር ሁሉ በተባዕት ጾታ መግለፁ ወንድትን የጥንካሬ አርማ በማድረግ ጾታን በተመለከት ሚዛናዊ መዛባትን በማህረሰቡ ምልክታ ላይ ያሳድራል፡፡ ከዚህም በላይ ፈጣሪን ሳይቀር ወንድ ብቻ እንደሆነ አድርጎ በመሳል የልዕልና ጥግ ላይ ወንድትን ያስቀምጣል (ያው ፈጣሪ መንፈስ እንደ መሆኑ ጾታ ሊኖረው እንደማይችል እሙን ነው)፡፡ በጥንት የነበሩ መንፈሳዊ ምልከታዎች እና አመለካከቶች የፈጣሪን ሴትነት እና ወንድነት (እንደ ሃይል ምንጭ) አድርገው ያምኑ እንደነበር የስነ-ሰብዕ እና የማህበራዊ ሳንይስ ተማራማሪዎች ይናገራሉ፡፡ ከአፍሪካ እንደ ዮሩባ ፣ ቮዱን ፣ዲንቃ ፣ኢግቦ፣ዳጎን እና በሌሎች እንደ ፣ግሪኮች፣ ፓጋን፣ አኒሚዚም፣ ሂንዱኢዘም፤ ካባሊዝም (ይሁዲዝም)፣ አዝቴኮችን ፣ እና ሌሎች ጥንታዊ ኃይማኖቶች የፈጣሪን ሴታዊ ህልውና በመቀበል በሀይማኖታዊ ልምምዶቻቸው ውስጥ ይተገብሩ ነበር፡፡
ሌላው ቋንቋ ላይ ካደሩ ተፅዕኖዎች መካካከል ወሲብ ቀስቃሽ ለሆኑ ነገሮች ሁሉ ሙሉ ለሙሉ እንስታይ ተውላጥ በመጠቀም ሴትን እንደ ወሲብ እቅ እንድናይ በማድረግ ሰብአዊ ክብርን የማሳነስ ተግባር ያስፋፋል፡፡ በርካታ ወንዶች ሴትን ሲያዩ ወሲባዊ ፍላጎት ይቀሰቀስባቸዋል (እኛን ባያካትትም :) ) ለምን አዕምሮአቸው ላይ የተሳለው ምስል ሴት ልጅ ለወሲብ ናት የሚል ለወንድም እርካታ ናት የሚል አመለካት በአባወራ መዋቅር የተፈጠረ አስተሳሰብ ስላለ ማለት ነው፡፡ ቀላል ስርአት አይደለም ምናወራው ጨቋኝ እና አሳናሽ የሆነ ጠባብ ግን ግዙፍ ነኝ ስለሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ለዘመናት ሴቶች የአባቷ ፣ የባሏ ፣ የወንድሟ ፣ የዘመድ ወንዶች፣ ንብረት እንደሆነች በማሰብ ማንነታቸው እዲያጡ እና ሰዋዊ ድምፃቸውን ተነጥቀው በባርነት ውስጥ እንዲኖሩ አስገድዷቸው ነበር ወንድ ሚስቱን ወይ ሴት ልጁን መሸጥ እስኪችል ማህረሰቡ እንደ መብቱ ይመለከት ነበር፡፡ ሀብት እንኳ ሲያከፋፍል ሴት ልጁ እስካትታሰብ ትረሳ ነበር የእራሷንም ሀብት ከማፍራ ትታገድ ነበር፡፡ የአባወራ ስርዓት ህልውናን የመንጠቅ እና የመሻር ስርዓት ነው፡፡
ሌላው ወሲብ ላይ ሲመጣ ሴት የራሷ ወሲባዊ ፍላጎት የሌላት ካላትም ወስላታ እና ሴሰኛ እንደሆነች በተቃራኒው ደግሞ ወንድ ወሲብ ላይ ፈጣን ከሆነ እና እንደ ጀግና በመሳል የበላይነትን የፈጠረ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ቀጥታ ተግባሩ ላይ ሲመጣ ‹በጂ›› ‹‹ተበጂ›› ‹‹መብዳት›› ‹‹መበዳት›› የሚሉ ቃላቶችን በመጠቀም የኃይል ተዋረድን በወሲባዊ ግንኙነት ላይ ይጭናል፡፡ ይህም በተቀባይነት ሚና ላይ ያለውን ሰው (ወንድ ሆነ ሴት) የበታች እንደሆነ አስተሳሰባዊ አድልዎን ይፈጥራል ይህ አስተሳሰብ እውነት አይደለም የሚለውን ለማየት ከፈለግን በተመሳሳይ ፆታ ወሲባዊ ተግባር ላይ ተቀባይ ሚና ሚጫወተውን ግለሰብ ከወንድነት እንደማነስ ተደርጎ ሲተች እንሰማለን ወንድነቱን እንደማሳነስ(መበዳት እንደ ማነስ ታይቶ ማለት ነው ስለዚህ ሴቶች ያንሳሉ ወንዶች ይበልጣሉ አይነት ሎጂክ ይከተላል) እና ሴትነትን እንደ መምረጥ አድረገው የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ የዚ አስተሳሰብ ስሩን ከተመለከትን ወንድ የሰጪነት ሚና ሲተገብር የበላይ የገዢነት ሚናን አብሮ እንደ ያዘ የሚያሳይ መግለጫም ነው፡፡ ችግሩ እዚ ጋ ነው ወሲብ የኃይል ተዋረድ፣ ወይም የበላይነት ማረጋጋጫ፣ የጀግንት መለኪያ ማን ገዢ ማን ተገዢ እንደሆነ ማሳያ መሆን አልነበረበትም የፍቅር መግለጫ እንጂ፡፡
በአባወራ ስርዓት ይህ ፍቅር ቦታ የለውም ፍቅር ተግባራዊ የሚሆነው ሁሉም በተሰመረለት ሚና ሳያዛንፍ ሲተግብር እና በዛ ሳጥን ውስጥ ተወስነን እስከተቀመጥን ብቻ ነው፡፡ ፍቅር ነፃ ስጦታ መሆኑ ይቀርና ደሞዝ ይሆናል፡፡
በሀገራችን ቋንቋ ፆታዊ ማንነትን ሆነ ጄንደርን እንዲሁም የተለያዩ ፆታዊ ዝንባሌዎችን ሊገልፅ የሚችል አዎንታዊ ቃላቶች ማግኘት እጅግ ከባድ ነው፡ በዚህም አናሳ ቁጥር ያላቸውን ግለሰቦች ሴቶች ሆኑ ወንዶች ቢሆኑ እንዲገለሉና መዋቅራዊ መድሎ እንዲደረግባቸው ይሆናል፡፡ ቋንቋ እንደ ስነ ልቦና አጥኚዎች ስለ ቋንቋ እና ስለ ተፅኖዎቹ ብዙ ፅፈዋል፡፡ አንድ ሰው በማህበረሰቡ ቋንቋ ስለ ማንነቱ እና ስለ እሱ የሚነገረው ነገር አሉታዊ ከሆነ የሚደርስት ስነልቦና ጫና ቃላት የሚገልፁት አይደለም:: ማንነቱን በአዎንታዊ መንገድ መግለጥ እስካይችል ለከፍተኛ የአዕምሮ እና ስሜታዊ ቁስለት ይዳርገዋል ራስ ወደ መጥላት እና ራስን እስከ መግደል ሊያደርሰው እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ምክንያቱም ይህ የአባወራ ስርዐዓት ለውስጠዊ ጭቆና የሚጋብዝ እና አፍናን እንደ መስሪያ የሚጠቀም ስለሆነ ነው፡፡
ይህን ስርዓት በመቃወም የተወለዱ ንቅንቄዎች
አንድ መዋቅር ለሺህ ዘመን ነበር ማለት ልክ ነው ማለት አይደለም ፤ ባህል አስተሳሰብ ሀይማኖት ሺህ ዘመን ነበር ማለት ዛሬ አስፈላጊ ነው ማለት አይደለም፡፡ ለዘመኑ የማይሆን ያፈጀ ስርዓት/መዋቅር መቀደድና መተው አለበት ይህን መቅደድ ደግሞ የእኛ ኃላፊነት ነው፡፡ አባወራ ስርዓት ዘመኑን ያማከለ እና ቀድሞም ጥቅም ነበረው ብሎ ለማመን የሚከብድ ነገር ነው፡፡ ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለወንዶችም ያልሆኑትን ማንነት እንዲላበሱ እና ሁሌ ጠንካራ በመሆን እንዲገኙ ስሜትን በማፈን ተጎጂ እንዲሆኑ እና በዚህ የታፈነ ስሜት የተነሳ ለአመፀኝነት ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋል (ሁሉ አመፀኝነት በዚ ይከሰታል ማለቴ ግን አይደለም)፡፡
ሴቶች ለራሳቸው መብት መታገል ሲጀምሩ ነበረውን እንውስቃሴ ፌሚኒዘም ብለን እንጠራዋለን አባወራ መዋቅር ሴቶች ላይ ያስቀመጠውን ከልካይ እና ጨቋኝ ቀንበር ለመደርመስ የተደረገ የትግል ንቅናቄ ነው አሁንም ድረስ ይህ ንቅናቄ የቀጠለ ሲሆን ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ጅምሮ የተጀመረ ስለ ሴቶች እኩልነት የሚታገል እንቅስቃሴ ነው፡ ሰው ሁሉ ፆታ ላይ ያልተመሰረተ እኩልነት አለው የሚል አስተሳሰብ ነው ፡፡ ወንድ ሴትም አካላዊ ልዩነታቸው ተቀብለው እኩል መታየት እና እኩል እድሎች ሊኖራቸው ይገባል የሚል ነው፡፡ ብዙ አይነት የፌሚኒዝም አስተሳሰቦች አሉ በሌላ ጊዜ ስለዛ ጠለቅ ያለ ዳሰሳ አቀርባለው፡፡
ሌላው የጥቁር መብት ንቅናቄ ነው ምንም እንኳ የነጭ የበላይነትን ለመቃመው እና ጥቁሮች እኩል መብት እንዲኖራቸው የሚናገር እንቅስቃሴ ቢሆንም ስሩን ስናጠናው ግን አስተሳሰባዊ ጭቆናን የመደብ መከፋፍን የሚቃወም እንቅስቃሴ እንደመሆኑ የአባወራ ስርዓት መደባዊ መሰረት ላይ የጣለውን መድልዎ ነቅሶ ለመደምሰስ የተደረገ እንቅስቀሴ ነው፡፡
የኩዊር መብት እንቅስቃሴ ይህ በፆታዊ ማንነታቸው እና ዝንባሌያቸው መገለል እና መድልዎ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ያደረጉት ትግል እንቅስቃሴ ሲሆን የራስ ማንነት በራስ የመበየን እና ጾታዊ ማንነትን በተመለከተ ግላዊ ነፃነትን ለማግኘት የተደረገ እንቅስቃሴ ነው ይህም በፖለቲካ ፣ በጤና ፣ በኢኮኖሚ ፣ ትዳር እና ማህበራዊ ዘርፎች ላይ ማንትን ሳይደብቁ እኩል ተሳታፊ እና ማንነታዊ እውቅና ማግኘት ብቻ ሳይሆን የመኖርን የመታየትን ሰብአዊ መብት ስለመጠየቅ ነው፡፡ በይዘቱ ከፌሚኒዘም ንቅናቄ ጋር የሚያዋስነው ነገር ስላለ 3ተኛው የፌሚኒዘም እንቅስቃሴ በርካታ ኩዊር የሆኑ ሰዎች በሁለቱም ንቅናቄዎች ላይ ነበሩበት፡፡ እንደ ሀገራችን ባሉ ማህረሰብ በርካታ ሰዎች ፌሚኒዝም ሴቶችን ሌዝቢያን የማድረግ እንቅስቀሴ ነው የሚል ስህተት የሆነ አመለካከት የተፈጠረባቸው ፡፡
የሰብአዊ መብት ትግል እንቅስቃሴዎች በማህረሰቡ መሃል እኩል ታይታን ለመፍጠር በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሰዎችን ሰብአዊ መብት ለማስጠበቅ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች ሲሆን:: ማሀብረሰባዊ፣ ባህላዊ፣ ብሔራዊ፣ ሀይማኖታዊ እና አመለካከታዊ እሳቤዎች በሙሉ ሰብአዊ መብትን የመወሰን ምንም አይነት መብት ሆነ ስልጣን እንደሌላቸው እና ሰብአዊ መብት ሰው በመሆናችን የምናገኛቸው መብቶች እንደሆኑ ይደነገግጋል፡፡ ታህሳስ 10፣ 1948 ኤ.አ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 30 አንቀዕ ያለውን አለም-አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ አፀደቁ ከእነዚ መሃል ኢትዮጵያ ዋነኛ የነበረች ሀገር ናት፡፡ የሰብአዊ መብት ንቅናቄ እነዚህ ህግጋት መጠበቃቸውን የሚያረጋግጥ ጥሰታቸውን ደግሞ አደባባይ የሚቃመው የእንቅስቃሴ አይነት ነው፡፡እነዚህ 30 አንቀፆች እያንዳንዱ እንደ ግለሰበው ሰው ሁሉ የእኩልነት፣ ሌሎችን እስካልጎዳ ድረስ ራሱን የመሆን ነፃነት ፣ ከመድልዎ መጠበቅ፣ የእውቅና፣ እና ሌሎችንም መብቶች የያዘ ሲሆን እንደ ኩዊር ግለሰቦች እና ሴቶች ያልነበራቸውን ነገር የሚያስጠብቅ ነው፡፡
ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ኩዊር ግለሰቦችን እንደ ሰው (ግለሰብ) እውቅና ስላልሰጡ ሙሉ ሰብአዊ መብታችን ብቻ ሳይሆን ሰዋዊ ክብራችን ህይወታችን ዋጋ የሌለው መስሎ እስኪታይ በገዛ ሀገራችን ላይ በችግር እና በመድልዎ እና ጭቆና አፈና እንድንኖር ተገደናል!!!
ለለውጥ ምን ማድረግ አለብን
ለለውጦች መካተት ያለባቸው ሚዲያ፣ በትምህርት መስኮች፣ ህጎች ላይ እንደሆነ ግልፅ ነው እነዚህ ነገሮች አስተሳሰብን ለመቅረፅ የማያወላዳ ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ እንደ ሀይማኖት እና ባህላዊ አስተሳሰቦች ህጋዊ ከለላ ሲኖር መከባበር እና መቻቻልን ይወልዳሉ፡፡ ባህል ደግሞ ይለወጣል ምክያንቱም ባህል ስለሰው እንጂ ሰው ስለባህል አልተፈጠረም፡፡ ህግ የተገለሉ እና አናሳ የማህበረሰብን ክፍል መጠበቅ ሲሳነው እና እነሱ ላይ ለሚደረጉ አመፃዎች ከለላ ማድረግ ሲሳነው ጥላቻ እና አለመቀበል ይበዛል፡፡ ይህን ለመቀየር እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የግድ እንደሆነ እሙን ነው፡፡
ነገር ግን እንደ ግለሰብ ምን ማድረግ እንችላለን የሚለውን ስንመለከት ተዋቂው የቻይና ፈላስፋ ኮንፊውሺየስ የተናገረውን መድገም ፍልጋው ‹‹ማህረሰቡ ላይ ያለውን ግፍ ለመቀየር የግድ ቤተመንግስት መገኘት አይጠበቅብኝም ይልቅ በአቅሜ በምሄድበት በማደርገው ነገር ሁሉ የምችለውን ለማድረግ እጥራለሁ›› ይለናል ያየናቸውን ፆታ፣ አካል፣ ዘር፣ ጾታዊ ዝንባሌ እና ሌሎች ነገሮች ላይ የተመሰረቱ በድሎዎችን በምናይበት ቦታ ተቃዋሚ እንሁን በመስሪያ ቤት ሊሆን ይችላል በቤተሰብ አባላት መሃል በሀይማኖት ተቋማት ብቻ የትም፣ መደብ የተመሰረተ መድልዎ መገለል ስናይ ከመናገር አንቆጠብ!
ከሁሉ በላይ ራሳችንን የተቀበልን፣ የምንወድ እና ለራሳችን ክብር ያለን እንሁን ይህ ሲሆን ሴሎችን ለማክበር ለመቀበል እና ለመደገፍ ውስጣዊ ኃይል ይኖረናል!!
ማጠቃለያ
ብዙ ብዙ ብንል የማያልቅ ግፍ፣ በደል እና አድልዎ ፣ጭቆና ፣አፈና በማህበረሰባችን ውስጥ አለ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ውጪውን ማሳመር እንጂ ውስጡን መጠበቅ ብዙ የማያስጨንቀው ለታይታ ብዙ ትኩረት የሚሰጥ ነው፡፡ በሚገርም ሁኔታ ደግሞ ማህበረሰባዊ፣ ሀይማኖታዊ መዋቅሩ የሚከተለው የአባወራ ስርዓታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህን ሁላችን ያደግንበት አስተዳደግ ወይም ባህል ማረጋገጫ ሆኖ መቅረብ እንደሚችል እንመሰክራልን፡፡ ባህሉ አስተሳሰቡ ይቀየር ማለት ሀገራችንን እንጠላለን ማለት አይደለም ይልቅ የተሻለ ሁሉን ማቀፍ፣ መቀበል እና ልዩነትን አክብሮ መቻቻል የሚችል ምንም ቅድመ ሁኔታ የሌለው እኩልነት ላይ የተመሰረተ ባህል የበለጠ ሰላማዊ ያደርገናል ለዘመኑም አስፈላጊ ነው ማለት ነው፡፡ አሁን ያለው አባወራዊ ባህልን መቃወም አባትን ከመጥላት ካለክማበር ወይም ወንድነትን ከመሻር አንጻር አይደለም (አንዳንዶች እንደሚሉት) ነገር ግን የሁሉም ሰው ታይታ እና ህልውና ሰላማዊ ፣ ነፃነታዊ እንዲሆን ከመፈለግ ነው፡፡


